Back to top

Sabbath Bible Lessons

የእውነት ውድ ሀብቶች (1) - ከፈጣሪያችን ጋር መወያየት

 <<    >> 
5ኛ ትምህርት ሰንበት፣ ጥር 27፣ 2015

ወንጌል በብሉይ ኪዳን

የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15፡4)

የሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣው ህዝቡን ከኃጢአታቸው ለማዳን ነው። እርሱ የኃጢአት አገልጋይ አይደለምና በኃጢአታችን አያድነንም። ለክርስቶስ መለኮታዊ ጥሪ ምላሽ ልንሰጥና ከኃጢአታችን ንስሐ መግባትና ቅርንጫፉ ከወይኑ ጋር አንድ እንደሆነ ራሳችንን ከክርስቶስ ጋር አንድ ማድረግ አለብን።”—The Signs of the Times, February 15, 1892.

ለጥናት የተመረጠው መጽሐፍ፡   አበዉ እና ነቢያት፣ ገጽ 63–70። 

እሁድ ጥር 21

1. ትምህርት ከታሪክ

ሀ. ታሪክን በተለይም ቅዱስ ታሪክን ማጥናት የሚያስፈልገን ዋናው ምክንያት ምንድን ነው? መክብብ 3:15

በእያንዳንዱ ታላቅ ተሐድሶ ወይም ሐይማኖታዊ እንቅስቃሴ፣ ከዘመን ዘመን እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚሰራው ሥራ አስደናቂ ተመሳሳይነት እንዳለው ያሳየናል። እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ግንኙነት የሚያካሂድባቸው መርሆዎች ሁል ጊዜም አንድ አይነት ናቸው። የዚህ ዘመን አስፈላጊ እንቅስቃሴዎች በፊት ከነበሩት ጋር የሚነፃፀሩ ናቸው፤ እናም በጥንት ዘመናት ቤተ ክርስቲያን የነበራት ተሞክሮ ለዚህ ለእኛ ዘመን ታላቅ ዋጋ የያዘ ትምህርት አለው።”—The Great Controversy, p. 343.

ለ. የታሪክ ጥናት የወንጌልን ተስፋ ስለሚያሰፋ (ሮሜ 15፡4) ይህ ተስፋ በኃጢአት ለታመመች ነፍስ ምን ይሰጣል? ሮሜ 1:16ሉቃስ 19፡10

እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በእግዚአብሔር መንፈስ የተሰጠና ጠቃሚም ነው። ብሉይ ኪዳን ከአዲሱ ያላነሰ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ብሉይ ኪዳንን ስናጠና ግድ የለሽ የሆነዉ አንባቢ ምድረ በዳውን ብቻ ሲመለከት እኛ የሕያዉ የሆኑ ምንጮች ሲፈልቁ እናገኛለን።”—ትምህርት፣ ገጽ. 213.


ሰኞ ጥር 22

2. የፍጥረት ፍፁምነት

ሀ. የመጀመሪያዎቹ ወንድና ሴት በፈጣሪያቸው እጅ ገና እንደተፈጠሩ ምን ዓይነት ባሕርይ ነበራቸው? ዘፍጥረት 1:31መክብብ 7፡29

ሰው በመልኩና በጸባዩ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠረ። ክርስቶስ ብቻ “የእግዚአብሔር ነጸብራቅ” ነዉ (ዕብራዊያን 1፡3)። ሰዉ ግን በእግዚአብሔር አምሳያ ተፈጠረ። ተፈጥሮዉም ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ስምሙ ነዉ። አዕምሮዉ መለኮታዊ ነገርችን ለመረዳት ይችላል። ስሜቶቹ ንጹህ ነበሩ ፍላጎቱም በዓላመዉ ቁጥጥር ሥር ነበር። የእግዚአብሔርን አምሳል በመልበሱ ቅዱስና ደስተኛ ለአምላካዊዉም ፈቃድ ፍጹም ታዛዥ ነበር።”—አበዉና ነቢያት፣ ገጽ. 36 (1)

ለ. የሰው ዘር በዚህ ፍጹም ሁኔታ ውስጥ ለዘላለም እንዲኖር ምን አስፈለገ? ዘፍጥረት 2:16፣ 17(ህዳግ)

ክርስቶስ የሕጉን ጥያቄዎችን አልቀነሰም። በማያሻማ ቋንቋ ለእርሱ መታዘዝን እንደ የዘላለም ሕይወት ቅድመ ሁኔታ አቅርቧል—በኃጢአት ከመውደቁ በፊት ከአዳም እንደሚፈለገው በተመሳሳይ ሁኔታ አቅርቧል። ጌታ በገነት ከሰው ከጠበቀው ከነፍስ ፍፁም ታዛዥነትና ነቀፋ ከሌለበትን ፅድቅ ያነሰ ነገር አሁን ከእኛ አይጠብቅም።

በጸጋው ቃል ኪዳን ሥር ያለው መስፈርት በኤደን ከተሰጠው መስፈርት ጋር ተመሳሳይ ነው—ቅዱስ፣ ጻድቅና መልካም ከሆነው ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር የሚስማማ ነው።”—Christ’s Object Lessons, p. 391

ሐ. ሰው ስለወደቀ/ኃጢአት ስለሠራ (ዘፍጥረት 3) በመጀመሪያ ወላጆቻችን ላይ ብቻ ሳይሆን በመላው የሰዉ ዘር ላይ ምን መዘዝ አስከተለ? ሮሜ 5:12፤ 6፡23

የእግዚአብሔርን ህግ በመታዘዝ ሰው እንደ ቅጥር ተከቦ ከክፋትም ይጠበቃል። ይህንን በመለኮታዊነት የቆመውን አጥር በአንድ ነጥብ የሚያፈርስ ማንም እርሱን ከክፉ የሚጠብቀዉን ኃይሉን ያጣል፤ ጠላት ሊያፈርስና ሊያጠፋ የሚገባበትን መንገድ ከፍቷልና።

በአንድ ነጥብ ላይ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ችላ በማለት፣ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በዓለም ላይ የወዮታን በሮች ከፍተዋል። እና የእነሱን ምሳሌ የሚከተል እያንዳንዱ ግለሰብ ተመሳሳይ ውጤት ያጭዳል። የእግዚአብሔር ፍቅር የሕጉን ትእዛዛት ሁሉ ይደነግጋል፣ ከትእዛዙም የሚርቅ የራሱን ሐዘንና ጥፋት በራሱ እጅ ይሠራል።”—Thoughts From the Mount of Blessing, p. 52.


ማክሰኞ ጥር 23

3. ኃጢአት ተገለፀ

ሀ. የአዳም መተላለፍ የእግዚአብሔርን ህግ መጣስ እንደሚጨምር እንዴት እናውቃለን? ሮሜ 7:7፤ ከዘጸአት 20:17፤ 1ኛ ዮሐንስ 3፡4

የእግዚአብሔር ህግ በሰዎች ላይ የአስገዳጅነት ዉጤት እንደሌለዉ የሚሰብኩ ወገኖች የእርሱን ሕግ ማክበር የማይቻል እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ እዉነት ቢሆን ኖሮ አዳም ሕጉን በመተላለፉ ስለምን ቅጣት ተቀበለ!የቀደሙት ወላጆቻችን ኃጢአት በዓለም ላይ ጥፋተኝነትንና ሐዘንን አስከተለ። እንደ እግዚአብሔር ቸርነትና እንደ ምህረቱ ባይሆንማ ኖሮ ሰበአዊዉ ዘር ተስፋ ቢስ ሆኖ በቀረ ነበር። “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነዉ” ሮሜ 6፡23። በሰዉ ልጆች አባት ላይ ቅጣት ከተበየነም በኋላ የእግዚአብሔር ሕግ ሊጣስ አይችልም።”—አበዉና ነቢያት፣ ገጽ. 56 (1)

ያለ ሕጉ ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ንጽህናና ቅድስና እንዲሁም ስለ ራሳቸው ኃጢአትና እድፍ ትክክለኛ መረዳት አይኖራቸውም። እውነተኛ የኃጢአተኛነት ስሜት አይኖራቸውም፤ የንስሐም አስፈላጊነት አይታያቸውም። የእግዚአብሔርን ሕግ ተላላፊ ሆነው የጠፉ መሆናቸው ስለማይታያቸው የሚያስተሰርየው የክርስቶስ ደም እንደሚያሻቸው አያስተውሉም። የመዳን ተስፋ ያለ ፍፁም የልብ ለውጥ ወይም ያለ ሕይወት ተሐድሶ ተቀባይነት ያገኛል። በእንዲህ ሁኔታ የላይ ላይ መለወጦች በስፋት ይንሰራፋሉ፤ ከክርስቶስ ጋር ፈጽሞ ህብረት አድርገው የማያውቁ እልፍ አዕላፋት የቤተ ክርስቲያን አባል ይሆናሉ።”—The Great Controversy፣ p. 468.

ለ. እነዚህን ጥቅሶች ስናነብ፣ የሱስ ከሕግ መተላለፍ ሊያድነን እንደመጣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያሳየው እንዴት ነው? ማቴዎስ 1፡21

የሱስ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ለማዳን ሞተ፣ በክርስቶስም መቤዠት ማለት የእግዚአብሔርን ሕግ መተላለፍ ትቶ ከኃጢአት ሁሉ ነጻ መውጣት ማለት ነው። በእግዚአብሔር ሕግ ላይ በጠላትነት የሚነሣሣ ልብ ከክርስቶስ ጋር የሚስማማ አይደለም፣ እርሱም በቀራንዮ መከራን ከተቀበለ በኋላ ሕጉን በአጽናፈ ዓለም ፊት ሕጉን ለማጽናትና ከፍ ከፍ ለማድረግ ከተሠቃየ ከክርስቶስ ጋር አይስማማም።”—Faith and Works, p. 95.

ህዝቡን ከህግ መተላለፍ ለማዳን የመጣ ድንቅ ወዳጅ የሱስ አለን። ኃጢአት ምንድን ነው? የኃጢአት ብቸኛ ፍቺ ሕግን መተላለፍ ነው። እንግዲህ እዚህ ላይ የሱስ ክርስቶስ ነው፣ በትክክል መጥቶ ጽድቁን ለእኛ የሚሰጠን፤ በእርሱ በማመን እንጂ በራሳችን ሃይል ማሸነፍ አንችልም። በየሱስ ክርስቶስ ካመንህ እርሱን ዛሬ ታገኘዋለህ። አሁን አዳኝህ እንደሆነ ማመን አለብህ፣ ምክንያቱም እሱ የሞተልህና ጽድቁን የሚቆጥርልህ፤ እሱ ለተጣሰው የእግዚአብሔር ህግ መስፈርቶች ሁሉ ታዛዥ በመሆኑ ነው። ይህን ካደረግህ፣ ስለ የሱስ ክርስቶስ የማዳን እውቀት ይኖርሃል። አዳምና ሔዋን ሕጉን ስለጣሱ ኤደን ገነትን አጥተዋል ነገር ግን አንተ ሕጉን ከተላለፍክ መንግሥተ ሰማያትን ታጣለህ።”—The Ellen G. White 1888 Materials, p. 128.


ረቡዕ ጥር 24

4. የአማኞች አባት

ሀ. ለምን የብሉይ ኪዳን አበዉ አብርሃም የአማኞች ሁሉ አባት በመባል ይታወቃል? ገላትያ 3፡6-9

የአብርሃም ፈተና በሰው ልጅ ላይ ሊመጣ ከሚችለው ፈተና ሁሉ እጅግ የከፋ ነው። በዚህም ፈተና ወድቆ ቢሆን ኖሮ የአማኞች ሁሉ አባት ተብሎ አይመዘገብም ነበር። ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ቢያፈነግጥ ኖሮ፣ ዓለም የማያጠራጥር እምነትና ታዛዥነትን የሚያሳይ አበረታች ምሳሌ ታጣ ነበር። ለእግዚአብሔር ሊሰጥ ከሚችለው በላይ ውድ ነገር እንደሌለ እንድንማር ትምህርቱ በየዘመናቱ እንዲበራ ተሰጥቷል። እያንዳንዱን ስጦታ ለአገልግሎቱ ጥቅም ላይ የሚውል፣ እንደ ጌታ ንብረት ስንመለከት ነው፣ ሰማያዊውን በረከት የምናገኘው። በአደራ የተሰጠህን ርስትህን ለእግዚአብሔር መልሰህ ስጥ፣ ብዙም አደራ ይሰጥሃል። ንብረቶቻችሁን ለራሳችሁ አኑሩ፣ ያኔ በዚህ ህይወት ምንም አይነት ሽልማት አታገኙም፣ የሚመጣውን ህይወት ሽልማትንም ታጣላችሁ።”—The SDA Bible Commentary [E. G. White Comments], vol. 1, p. 1094.

መቅደሱ የተገነባበት ቦታ ለረጅም ጊዜ እንደ የተቀደሰ ቦታ ይቆጠር ነበር። ቦታዉም የአማኞች ሁሉ አባት አብርሃም ለእግዚአብሔር ትዕዛዝ በመታዘዝ ብቸኛዉን (አንዲያ) ልጁን መስዋዕት ለማድረግ ፈቃዱን ያሳየበት ቦታ ነበር። እዚህ ላይ አምላክ ከአብርሃም ጋር የበረከት ቃል ኪዳንን አድሶ ነበር፤ እሱም በልዑል ልጅ መሥዋዕት አማካኝነት ለሰው ልጆች የሚሰጠውን ክቡር መሲሐዊ ተስፋን ይጨምራል።”—Prophets and Kings, p. 37.

ለ. የዘሩ ተስፋ በአብርሃም ዘመን እንኳን የወንጌልን ስብከት የሚያሳየው እንዴት ነው? ዘፍጥረት 22:15–18ገላትያ 3፡16

የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ የሚለው ቃል ኪዳን ለአብርሃም ታደሰ። ዘፍጥረት 22፡18 ይህ ተስፋ ክርስቶስን ያመለክታል። ስለዚህም አብርሃም ተረድቶታል (ገላትያ 3፡8, 16 ተመልከት)፣ እናም ለኃጢአት ይቅርታ በክርስቶስ አምኗል። ይህ እምነት ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳንም የአምላክን ሕግ ሥልጣንን አስጠብቆታል።”—አበዉና ነቢያት፣ ገጽ. 370.

ሐ. አብርሃም ወንጌልን የተቀበለ ተብሎ ተለይቷል፣ እና በዘመኑ የነበሩት ሌሎች ብዙዎች ግን እንደዚህ አልተባሉም፤ ለምን? ዘፍጥረት 26:5ያዕቆብ 2፡19-24

አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ። ማመኑን እንዴት እናውቃለን? ሥራው የእምነቱን ባሕርይ ይመሰክራል፣ እምነቱም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።The SDA Bible Commentary [E. G. White Com-ments], vol. 7, p. 936


ሐሙስ ጥር 25

5. ሕግ በቀሪው የብሉይ ኪዳን ክፍሎች

ሀ. ሕጉ እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ቃል በቃል ከመናገሩ በፊት እንደነበረ ሌላ ምን ምሳሌዎች አሉን? (ዘዳ 5፡22-26) ዘጸአት 15:26፤ 16፡28።

እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበራቸው ረጅም ጉዞ በየሳምንቱ በሚያደርጉት ጊዜያዊ ቆይታ የሰንበትን ቅዱስነት እንዲያስተዉሉ ለማድረግ በዕለቱ ሦስት እጥፍ ተዓምራቶችን እንዲታዘቡ ይደረጉ ነበር። ከወትሮዉ እጥፍ መጠን ያለዉ መና በስድስተኛዉ ቀን ሲወርድላቸዉ በሰንበት ቀን ግን አንድም አይኖርም። ለሰንበት ቀን የሚያስፈልጋቸዉ መጠን ጣፋጭና ንጹህ ሆኖ ይቆያቸዉ የነበረ ሲሆን፤ ነገር ግን በሌሎቹ የሳምንቱ ቀናት በዕለቱ የሰበሰቡትን መና ለቀጣዩ ቀን ቢያስቀምጡ ይበላሽባቸዉ ነበር።

ለእስራኤላዊያኑ ይወርድ ከነበረዉ መና በተያያዘ መመለከት እንደምንችለዉ አንዳንዶች እንደሚሉት ሰንበት የተቋቋመዉ ትዕዛዛቱ በሲና በተሰጡ ጊዜ አልነበረም። እስራኤላዊያን ወደ ሲና ከመምጣታቸዉ አስቀድሞ ሰንበት በእነርሱ ላይ አስገዳጅነት እንዳለዉ አስተዉለዋል። ሰንበት ዝግጅት ሲያደርጉ አርብ ዕለት እጥፍ መሰብሰባቸዉና በነጋታዉ ከሰበሰቡት አንዱም ተበላሽቶ አለመጣሉ፤ ቅዱስ የሆነዉ የእረፍት ቀን ተፈጥሮ ያለማቋረጥ በአዕምሮአቸዉ ተጽዕኖ አድርጎባቸዉ ነበር። ከሕዝቡም አንዳንዶቹ መና ሊሰበስቡ በሰንበት በወጡ ጊዜ ጌታ ፡- “ትእዛዜንና ሕጌን ለመፈጸም እስከ መቼ እምቢ ትላላችሁ?” ሲል ሙሴን ጠየቀዉ።”—አበዉና ነቢያት፣ ገጽ. 331 (1)

ለ. አምላክ እስራኤላዊያን በንግግርና በጽሑፍ የሰፈረውን የአሥርቱ ትእዛዛት የሥነ ምግባር ሕግ ምን እንዲያደርጉ አስቦ ነበር? ዘዳግም 6:1-9

ሐ. ጌታ ይህንን አቋም እስከ ብሉይ ኪዳን መጨረሻ ድረስ እንደጠበቀው እንዴት እናውቃለን? ሚልክያስ 4:4፤ 3፡6።


አርብ ጥር 26

የግል የግምገማ ጥያቄዎች

1. የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መሠረታዊ ሥርዓቶች በእኛ ጊዜ የሚሠሩት እንዴት ነው?

2. አምላክ እንደማይለወጥ የሚያሳየው ከኤደን ወዲህ ምን መሥፈርት ነው?

3. ከኃጢአት ችግር ጋር በተያያዘ የሱስ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ዓላማ ምንድን ነው?

4. የአብርሃም እምነት በሥራው የተገለጸው እንዴት ነው?

5. ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ያለን ግንኙነት ምን መሆን አለበት?

 <<    >>