Back to top

Sabbath Bible Lessons

የእውነት ውድ ሀብቶች (1) - ከፈጣሪያችን ጋር መወያየት

 <<    >> 
2ኛ ትምህርት ሰንበት፣ ጥር 6፣ 2015

ኃያሉ የእግዚአብሔር ቃል

የመታሰቢያ ጥቅስ፡- አቤቱ፥ ንጹሕ ልብን ፍጠርልኝ፥ የቀናውንም መንፈስ በውስጤ አድስ።” (መዝሙረ ዳዊት 51፡10)

አብዛኛውን ጊዜ ፈተናዎች መቋቋም የማይቻሉ ይመስላሉ፤ ምክንያቱም ፀሎትንና የመጽሐፍ ቅዱስን ጥናት ቸል በማለቱ ተፈታኙ ሰው የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ወዲያውኑ አስታውሶ በመጽሐፍ ቅዱስ [ጥቅስ] መሳሪያዎች ሰይጣንን መፋለም ስለማይችል ነው።”—The Great Controversy, p. 600.

ለጥናት የተመረጠው መጽሐፍ፡   Fundamentals of Christian Education, pp. 123–128 

እሁድ ታህሳስ 30

1. የመስቀሉ ወታደሮች

ሀ. በምድር ላይ በምንኖርበት ጊዜ ሁልጊዜ ምን ማወቅ አለብን? 1ኛ ጴጥሮስ 5:8 ታዲያ ጳውሎስ የአንድን ክርስቲያን ሕይወት እንዴት ያወዳድራል? 2ኛ ጢሞቴዎስ 2:3

ባዶነቷ ከሚሰማትና ሙሉ በሙሉ በተሰቀለውና በተነሳው አዳኝ ደም ትሩፋቶች ላይ ከምትታመን ነፍስ በላይ ማንም፤ ምንም ነገር ማድረግ የማይችልና ረዳት አልባ ሊሆን አይችልም። የክርስትና ሕይወት የጦርነት፣ የማያቋርጥ የግጭት ሕይወት ነው። ጦርነትና ሰልፍ ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ ለክርስቶስ የመታዘዝ ተግባር፣ ለእርሱ ሲል ራስን የመካድ ተግባር፣ እያንዳንዱ የምንታገሰዉ ፈተና፣ እያንዳንዱ በፈተና ላይ የተገኘ ድል፣ የመጨረሻው የድል ክብርን ለማግኘት የሚደረግ ጉዞ አካል ነው።—That I May Know Him, p. 253.

ለ. በመጨረሻ አሸናፊዎች የምንሆነው እንዴት ስናደርግ ብቻ ነው? ኤፌሶን 6፡11-17

የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ የሚለብሱ እና ለማሰላሰልና ለጸሎት እንዲሁም ቅዱሳት መጻሕፍትን በማጥናት በየቀኑ የተወሰነ ጊዜ የሚያጠፉ ከሰማይ ጋር ይገናኛሉ እናም በዙሪያቸው ባሉት ሰዎች ላይ የሚያድንና የሚቀይር ተጽእኖ ይኖራቸዋል። ታላቅ ሀሳቦች፣ የተከበሩ ምኞቶች፣ ስለ እውነትና ለእግዚአብሔር ስላለዉ ግዴታ ግልጽ ግንዛቤዎች ይኖሯቸዋል። ... እነዚህም ወሰን አልባ ወደሆነው ፊት ለመቅረብ የተቀደሰ ድፍረት ይኖራቸዋል። የሰማይ ብርሃንና ክብር ለእነሱ እንደሆነ ይሰማቸዋል፣ እናም በዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ቅርርብ የነጠሩ፣ ከፍ ያሉና የተከበሩ ይሆናሉ። ይህም የእውነተኛ ክርስቲያኖች ልዩ ጥቅም ነው።”— Testimonies for the Church, vol. 5, pp. 112, 113


ሰኞ ጥር 1

2. ኃይል በቃሉ ውስጥ

ሀ. ቃሉ በእውነት ወደ ነፍስ ሲገባ ምን ያህል ዘልቆ ይገባል? ዕብራውያን 4፡12

በልብ ውስጥ የሚታሰቡ የመነሳሳት ቃላት ከሕይወት ውሃ ወንዝ እንደሚፈስሱ ጅረቶች ይሆናሉ። ቅዱሳት መጻሕፍትን ለመረዳት የደቀ መዛሙርቱ አእምሮ እንዲከፈት መድኃኒታችን ጸለየ። በጸሎት ልብ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና፣ መንፈስ ቅዱስ የምናነበውን ቃል ትርጉም ሊከፍትልን ቅርብ ነው።”— Our High Calling, p. 205.

እውነት በተግባር ወደ ሕይወታችን መምጣት አለበት፣ እና ቃሉ፣ እንደ የተሳለ፣ ሁለት አፍ እንዳለው ሰይፍ፣ በባህሪያችን ውስጥ ያለውን ትርፍ ቆርጦ ማውጣት አለበት።

ቃሉ ትዕቢተኞችን ትሑታን፣ ጠማማዎችን የዋሆችና የሚጸጸቱ፣ የማይታዘዙትን ታዛዥ ያደርጋቸዋል። በሰው ላይ የሚፈጠሩት የኃጢአተኛ ልማዶች ከዕለት ተዕለት ተግባር ጋር የተሳሰሩ ናቸው። ቃሉ ግን የሥጋን ምኞት ይቆርጣል። የአዕምሮ ሃሳቦችንና ዝንባሌዎችን የሚለይ ነው። ጅማትንና ቅልጥምንም ይከፋፈላል፣ የሥጋን ምኞት ያስወግዳል፣ ሰዎችንም ለጌታቸው መከራ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዲሆኑ ያደርጋል።The SDA Bible Commentary [E. G. White Com-ments], vol. 7, p. 928.

ለ. በመጀመሪያ ቃሉ ሰማይንና ምድርን በምን ያህል ፍጥነት ፈጠረ? ዘፍጥረት 1:1፤ መዝሙረ ዳዊት 33:6፣ 9

ሐ. እግዚአብሔር ቃሉን ተጠቅሞ ዓለማትን የፈጠረው ከየትኛው ቁሳቁስ ነው? ዕብራውያን 11፡3 ዓለማትን ከፈጠረ በኋላ እግዚአብሔር ፍጥረታት ራሳቸዉን እንዲጠብቅ ተዋቸዉን? ዕብራውያን 1፡3

ዓለምን ወደ ሕልውና ያመጣው ያው ፈጠሪ ሃይል አሁንም አጽናፈ ሰማይን በመደገፍና የተፈጥሮን ስራዎች ለማስቀጠል ይተጋል። የእግዚአብሔር እጅ ፕላኔቶችን በሰማያት ላይ በሥርዓት ሲጓዙ ይመራቸዋል። ምድር ከአመት አመት በፀሀይ ዙሪያ እንቅስቃሴዋን የምትቀጥልበትና ችሮታዋን የምታፈራው በተፈጥሮ ሃይል አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል ንጥረ ነገሮችን ይቆጣጠራል። ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል ለምድርም ዝናብን ያዘጋጃል፤ ሣርን በተራሮች ላይ ያበቅላል። መዝሙረ ዳዊት 147:8 ዕፅዋት የሚበቅሉት፣ ቅጠሎቹ የሚወጡትና አበቦቹ የሚያብቡት በእሱ ኃይል ነው።”—Counsels to Parents, Teachers, and Students, pp. 185, 186.


ማክሰኞ ጥር 2

3. ኃጢአትን አምኖ መቀበል (እዉቅና መስጠት)

ሀ. ዳዊት በእግዚአብሔርና በቤርሳቤህ ላይ ኃጢአት ከሠራ በኋላ ምን ፈልጎ ነበር? መዝሙረ ዳዊት 51:1-4

ለ. ዳዊት የተናገራቸውን የንስሐ መግለጫዎች በመለኮታዊ መዝገብ ውስጥ ተጠብቀው ቆይተዋል፤ እነዚህም በጣም ያሳሰበው ይኸውም የሚያጋጥመውን መዘዝ ወይም ከአምላክ ጋር ያለውን ዝምድና ማደስ? መዝሙረ ዳዊት 51:5-10

የእግዚአብሔርን መከፋት የሚሳይ ዉጫዊ ማስረጃ ባለመኖሩ፤ ዳዊት ከዉድቀቱ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል በተሸለ የደህንነት ስሜት የኖረ መሰለ። ነገር ግን መለኮታዊ ፍርድ በላዩ እያንዣበበ ነበር። ንስሃ የማይቀለብሰዉ፣ ምድራዊ ሕይወቱን አጨልሞ ሐፍረትና መሸማቀቅ የሚያስከትል ፈጣንና እርግጠኛ የፍርድና የበቀል ቀን እየተቃረበ ነበር። የዳዊትን ምሳሌነት እየጠቀሱ ኃጢአታቸዉን ለማቃለል የሚሞክሩ ሁሉ የመተላለፍን ጎዳና ከባድነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች መማር ይችላሉ። ምንም እንኳን እንደ ዳዊት ከክፋት መንገዳቸዉ መመለስ ቢኖርባቸዉም፤ የኃጢአትን ዉጤት መሸከም ከባድና መራር ነዉ።”—አበዉና ነቢያት፣ ገጽ 400

የዳዊት ንስሐ ጥልቅና ከልብ የተደረገ ነበር። ወንጀሉን ለማቃለል ምንም ጥረት አላደረገም። ከሚያስፈራዉ ፍርድ ለማምለጥ ምኞት ያልነበረዉ ዳዊት የተላለፈዉን አምላካዊ ሕግ ስፋትና ጥልቀት ተመልክቷል። የነፍሱን መቆሸሽ አስተዉሏል፣ ኃጢአቱንም ተጸይፏል። የጸለየዉ ምህረት ለማግኘት ብቻ ሳይሆን የልብ ንጽህናን ለማግኘት ጭምር ነበር። በትግሉ ተስፋ ያልቆረጠዉ ዳዊት፤ እግዚአብሔር ለተጸጸቱ ኃጢአተኞች በገባዉ ቃል መሠረት ይቅር መባሉንና በጌታ ፊት ተቀባይነት ማግኘቱን አረጋግጧል።”—ኢቢድ፣ ገጽ. 403

ዳዊት በንስሐና በጸጸት ልቡን በእግዚአብሔር ፊት ስላዋረደና እግዚአብሔር ይቅር ለማለት የገባው ቃል እንደሚፈጸም ስላመነ በደሉ ይቅርታ ተደረገለት። ኃጢአቱን ተናዞ፣ ተጸጸተ፣ እናም ተመለሰ። ይቅርታ እንደተደረገለት ሲያረጋግጥ በደስታ፣ “መተላለፉ የቀረችለት ኃጢአቱም የተከደነችለት ምስጉን ነው። እግዚአብሔር በደልን የማይቈጥርበት በመንፈሱም ሽንገላ የሌለበት ሰው ምስጉን ነው። መዝሙር 32:1፣ 2 በረከቱ የሚመጣው በይቅርታ ነው፤ ይቅርታ የሚመጣው የተናዘዝነው እና የተፀፀትንበት ኃጢያት በታላቁ ኃጢያት ተሸካሚ ላይ እንደሚሆነ ስናምን ነው። ስለዚህ በረከታችን ሁሉ ከክርስቶስ ነው። የእርሱ ሞት ለኃጢአታችን ማስተሰረያ መስዋዕት ነው። እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረትና ሞገስ ያገኘንበት ታላቁ መካከለኛ ነው።”— Our High Calling, p. 83.


ረቡዕ ጥር 3

4. የሰውን ልብ የሚለወጥ ኃይል

ሀ. የረከሰውን፣ የኃጢአተኛ ሕይወትን ወደ ንጽህና የመለወጥ ዕድል ምን ተስፋ ይሰጣል? ኢዮብ 14:4ኤርምያስ 13:23ሕዝቅኤል 36:26፣ 27

እርግጥ ነዉ ያለ ክርስቶስ ለዋጭ ኃይል ዉጫዊ የባሕርይ መልካምነት ሊኖር እንደሚችል አይካድም። በሌሎች ለመታየትና ለመወደስ ያለን ፍላጎት የተስተካከለ የምንለዉን ሕይወት እንድንቀዳጅ ሊያተጋን ይችላል። ለራሳችን ያለን አክብሮት የክፋት መገለጫ እንዳንሆን ሊያግዘን ይችል ይሆናል። ምናልባት ራስ ወዳድ ልብ ለሌሎች መልካም ነገርን ሊያደርግ ይችል ይሆናል። ታዲያ ከማን ወገን እንደሆንን የሚወስነዉ በምን መንገድ ነዉ?”—ወደ ክርስቶስ የሚያመራ መንገድ፣ ገጽ. 54.

እግዚአብሔር በዓለም ላይ ካለው ክፉ ነገር ጋር ለመዋጋት የተትረፈረፈ ዘዴ አዘጋጅቷል። መጽሐፍ ቅዱስም ለትግሉ የምንታጠቅበት የጦር ዕቃ ቤት ነው።”—The Acts of the Apostles, p. 502.

ለ. የተበላሸ የሰው ልብ በጽድቅ ወደሚደሰት ልብ የሚለወጥበት ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው? ዮሐንስ 3፡3

ቀድሞ ይጠሏቸዉ የነበሩ ነገሮችን አሁን ይወዳሉ፤ ቀድሞ ይወዷቸዉ የነበሩ ነገሮችን አሁን ይጠላሉ። በራሳቸዉ ብቻ የሚታመኑ ልበ ደንዳኖች የነበሩ ትሁትና የተሰበረ ልብ ባለቤት ይሆናሉ። ግብዝነትና ልታይ ባይነት በእዉነተኛነትና በጭምትነት ይተካል። የመጠጥ ሱሰኛዉ ከነበረበት የመጠጥ ሱስ ይላቀቃል፣ አባካኞች ከማባከን ይታቀባሉ።”—ወደ ክርስቶስ የሚያመራ መንገድ፣ ገጽ. 54.

ሐ. የዚያ ለውጥ ማስረጃዎች ምንድን ናቸው? ገላትያ 5:22፣ 23

ከደምና ከሥጋ ፈቃድ የተወለደ አሮጌው ተፈጥሮ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊወርስ አይችልም። አሮጌው መንገዶች፣ የዘር ውርስ ዝንባሌዎች፣ የቀድሞ ልማዶች መተው (መቅረት) አለባቸው፤ ጸጋ አይወረስምና። አዲስ ልደት አዲስ ተነሳሽነት፣ አዲስ ጣዕምና አዲስ ዝንባሌዎች መኖርን ያጠቃልላል። በመንፈስ ቅዱስ ለአዲስ ሕይወት የተወለዱት፣ የመለኮታዊ ተፈጥሮ ተካፋዮች ሆነዋል፣ እና በሁሉም ልማዶቻቸው እና ልምምዳቸው ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማረጋገጫ ይሰጣሉ። ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በተፈጥሮአቸው የባሕርይና የአመለካከት ድክመቶቻቸውን ከያዙ አቋማቸው ከዓለማዊው በምን ይለያል? እውነትን እንደሚቀድስና እንደሚያጠራ አምነዉ አላደነቁም። ዳግመኛ አልተወለዱም።”—The SDA Bible Commentary [E. G. White Comments], vol. 6, p. 1101.


ሐሙስ ጥር 4

5. በእግዚአብሔር ቃል የተወለደ

ሀ. በተንኮለኛና ክፉ ሰው ልብ ውስጥ እንዲህ ያለ ሥር ነቀል ለውጥ ለማድረግ ኃይል ያለው ምንድነዉ? ሮሜ 1:16ዮሐንስ 1:1፤ 15:3፤ 1ኛ ጴጥሮስ 1፡23

መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ ሁሉ የሚበልጥ ድንቅ ነው፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር እንጂ የውስኑ የሰዉ አእምሮ ዉጤት አይደለም። ያለበለዚያ ፈጽሞ ሊታወቅ የማይችለዉን የዘመናት ትዕይንቶችንኛ ታሪክ እያቀረበ በዘመናት ውስጥ ወደ ሁሉም ነገር መጀመሪያ ሊያደርሰን አይችልም ነበር። የወደቀውን ዓለም ለማዳን በሚያደርገው ጥረት የእግዚአብሔርን ክብር ይገልጣል። በቀላል ቋንቋ ሰዎችን ከሰይጣን ሠረገላ ጋር የሚያስረውን ሰንሰለት የሚቆርጥበትን የወንጌል ኃይል ይሰጣል።—Fundamentals of Christian Education, p. 377

ለ. ቃሉ በውስጣችን የሚቀሰቅሰው ምንድን ነው? ይህስ ለድል አድራጊ ሕይወት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ሮሜ 10:17፤ 1ኛ ዮሐንስ 5፡4 ለቀሪው ሕይወታችን ያንኑ ዓይነት ድል እንዴት እንጠብቀዋለን? ቆላስይስ 2፡6

የእዉነት መርሆችን በእምነት ተቀብለን ከሕልዉናችን ጋር ስናዋሕዳቸዉ የሕይወታችን አንቀሳቃሽ ኃይል ይሆናሉ። የእግዚአብሔር ቃል ወደ ልብ ሰርጾ ሲገባ ሀሳብን ያስተካክላል ባሕርይንም ያዳብራል።

ያለማቋረጥ በኃይማኖት ዓይን የሱስን በመመለከት ጥንካሬ እናገኛለን። እግዚአብሔር እዉነትን ለተራቡትና ለተጠሙት ልጆቹ እጅግ የተከበረዉን ምስጥሩን ይገልጥላቸዋል። የሱስ የግል አዳኝ መሆኑን ይረዳሉ። ቃሉን እንደተመገቡ መጠን መንፈስና ሕይወት መሆኑን ይገነዘባሉ። ቃሉ ተፈጥሯዊና ምድራዊዩን ባሕርይ ደምስሶ በየሱስ ክርስቶስ አዲስ ሕይወትን ይሰጣል። ቅዱስ መንፈስም ነፍስን ለማጽናናት ይመጣል። የመለወጥ ኃይል ባለዉ ጸጋዉ አማካይነት የእግዚአብሔር ምስል በደቀ መዝሙሩ ላይ ስለሚቀረጽ አማኙ አዲስ ፍጡር ይሆናል። ይህ ሲሆን በጥላቻ ፋንታ ፍቅር ይተካል፣ ልብም የመለኮትን ምሳሌነት ይይዛል።”—የዘመናት ምኞት፣ ገጽ. 397.


አርብ ጥር 5

የግል ግምገማ ጥያቄዎች

1. ክርስቲያን ከክፉ ጋር የሚያደርገው ጦርነት ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

2. ቃሉ በዚህ ጦርነት ውስጥ ምን ጠቃሚ ቦታ አለው?

3. የኃጢአትን አጥፊ ተፈጥሮ ጥልቀት እንዴት መረዳት ይቻላል?

4. የነፍስ ለውጥ እንዴት ይከናወናል?

5. ከክርስቶስ ጋር ያለንን ዝምድና ማቆየት የምንችለው እንዴት ነው?

 <<    >>